የመጀመሪያው “ድሬ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ” በድሬዳዋ ሊከናወን መሆኑ ተገለፀ

2023-09-26
Event Image

የመጀመሪያው “ድሬ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ” በድሬዳዋ ሊከናወን መሆኑ ተገለፀ

 

(መስከረም 16,2016)

 

በክልሎች ደረጃ በአይነቱ እና በይዘቱ ቀዳሚ እንደሆነ የተነገረለን “1ኛው ድሬ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ” (1st Dire International Tech Expo) በድሬዳዋ ከተማ ሊከናወን መሆኑ ተገለፀ። 

መስከረም 16 ቀን 2016 በድሬዳዋ ከተማ በተዘጋጀው የመግባቢያ  ሰነድ ፊርማ ሥነ-ስርዓት ላይ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት እና ማኔጅመንት ኃላፊና የክቡር ከንቲባ ተወካይ ኢንጂነር  ሳጂድ ዓሊዬ እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ሹክሪ ዐአብዱረህማን ከአዘጋጁ ስካይሊንክ ቴክኖሎጂስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሐመድከረም አህመድ ጋር በጋራ በመሆን የኤክስፖውን መጀመር በይፋ አብስረዋል። 

ከጥር 15-19 ቀን 2016 እንደሚከናወን የተገለፀው ይህ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሰማሩ አገር በቀል እና የውጭ ተቋማት በስፋት እንደሚሳተፉበት ተጠቁሟል። 

በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይና የአስተዳደሩ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ኢንጂነር ሳጅድ አልዪ  የኤክስፖውን አዘጋጆች አመስግነው፤ በከተማችን ድሬዳዋ እንደነዚህ አይነት ኤክስፖዎች መዘጋጀታቸው በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። 

ኢንጂነር ሳጅድ  አክለውም ከተማችን ድሬዳዋ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ይሄንን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደነዚህ አይነት ኤክስፖዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል። የመስተዳደሩ ወጣቶችም በዚህ ኤክስፖ ላይ በነቂስ በመሳተፍ ያላቸውን አቅም ለአለም ማሳየት እንደሚገባቸውም ገልፀዋል። 

የኤክስፖው ዋና አዘጋጅ የሆነው ስካይሊንክ ቴክኖሎጂስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሐመድከረም አህመድ እንደገለፁት አገራችን ዘመኑ ከሚጠይቀው የቴክኖሎጂ ልህቀት ጋር በእኩል ለመራመድ የጀመረችውን ግስጋሴ እንደሚያግዝ  የታመነበትና የድሬዳዋን የቀደመ ስም ዳግም ህያው የሚያደርግ  “የመጀመሪያው ድሬ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ” “1st Dire International Tech Expo” በሚል ታላቅ የቴክኖሎጂ ድግስ መዘጋጀቱንና የኤክስፖው መሪ ቃል “Idea to Reality” (ሃሳብን ወደ እውነታ) ሆኖ እንደተመተጠ አስረድተዋል።  

አክለውም “ይህ ዝግጅት በዓይነቱ ለድሬደዋ አዲስ የሆነና በውጤቱ ድሬደ‍ዋን የአገሪቱ የቴክኖሎጂ ማዕከል ሆና እንድትገኝ የሚያግዝ የመጀመሪያ እርምጃ ነው።”ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳዳር ከንቲባ ጽ/ቤት የካብኔ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ  ወ/ሮ ሹኩሪ አብዱረማን በበኩላቸው በፕሮግራሙ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ ከተማችን ድሬዳዋ የምስራቅ ኢትዮጵያ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የመግቢያ በር፣ በሀገራችን ትልቁ የኢንደስትሪ ፖርክ እንዲሁም ደረቅ ወደብ መገኛ መሆኗን አንስተው ይህም ከተማዋን ለቴክኖሎጂና ለንግድ ስራ አመቺ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል። ይህንን አለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ባዛርና ሲንፖዚየም ለማዘጋጀትም ከተማችን ድሬዳዋ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ወ/ሮ  ሽኩሪ ገልፀዋል። 

ዝግጅቱ ድሬደዋ የአገሪቱ የቴክኖሎጂ ማዕከል ሆና እንድትገኝ የሚያግዝ የመጀመሪያ እርምጃ እንደሆነና በኤክስፖውም አገር በቀል የሆኑ የቴክኖሎጂ አገልግሎት አቅራቢዎች፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ የግሉ እና የመንግስት ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት እና የቴክኖሎጂ ግብዓት አቅራቢዎች፣ ልዩ የሆኑ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ባለሞያዎች፣ የቴክኖሎጂ አገልግሎት ፈላጊ የሆኑ ተቋማት እና ግለሰቦች፣ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም የትምህርት እና የምርምር ተቋማት  በዚህ ታላቅ ኤክስፖ ላይ በስፋት እንደሚሳተፉም የስካይሊንክ ቴክኖሎጂስ ሥራ አስፈፃሚ ገልፀዋል። 

ኤክስፖው ከጥር 15 እስከ ጥር 19 ድረስ በግዙፉ ወጣቶች ስፖርት ማዕከል እንደሚካሄድና ከሁሉም ክልል የሚመጡ 200 የመንግስት እና የግል ድርጅቶች፣ 100 የሚደርሱ የውጭ አገር የቴክኖሎጂ ተቋማት እንዲሁም ከ50 በላይ ኢንተርፕራይዝ ድርጅቶች እንደሚሳተፉበት ከመድረኩ ተነግሯል። 

እዚህ ኤክስፖ ላይ የሚሳተፉ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ባሉበት ሆነ ኤክስፖውን አስመልክቶ ሙሉ መረጃ የሚያገኙበትን direinttechexpo.com የተሰኘውን የዲጅታል ፖርታል እንዲጎበኙ እና ምዝገባውንም በዚያው ፖርታል ላይ እንዲያደርጉ እንዲሁም በኢሜል info@direinttechexpo.com  መመዝገብ እንደሚችሉም አቶ ሙሐመድከረም አብራርተዋል።

በመጨረሻም አቶ ሙሐመድከረም ለዚህ በክልል ደረጃ የመጀመሪያ የሆነው የድሬ ኢንተርናሽናል ቴክኖሎጂ ኤክስፖ እውን ይሆን ዘንድ ፈር ቀዳጅ ለሆነው የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

ይህ ኤክስፖ ለ5 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን በቆይታውም ከ40,000 በላይ ጎብኚዎች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል። 

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር መገንባትን ተከትሎ በ1902 የተወለደችው ድሬዳዋ፣ የዘመናዊ የኢትዮጵያ ንግድ ፣ኢንቨስትመንት ፣ቴክኖሎጂ እና የተለያዩ ዘመን አይሽሬ ኢንዱስትሪዎች የትውልድ ሥፍራ መሆኗ ያለፈ ታሪኳ ያስረዳል።