የመጀመሪያው ድሬ ዓለም ዓቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በመጪው ጥር ይካሄዳል

2023-11-19
Event Image

"ድሬ ዓለም ዓቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ" በመጪው ጥር ይካሄዳል
ፕራይም ሚዲያ(አዲስ አበባ)_የመጀመሪያው "ድሬ ዓለም ዓቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ" ከመጪው ጥር 15 እስከ ጥር 19 ድረስ "ከሃሳብ ወደ ትግበራ" በሚል መሪ ቃል በድሬዳዋ ከተማ ይካሄዳል ።
ይህንንም አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በኢንተር ለግዠሪ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል ።
በመግለጫው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ድሬዳዋ ቀደምትነቷን የሚመጥን ደረጃ ላይ ለመድረስ እንድትችል እየተሰራ ላለው ስራ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው ብለዋል ።
አክለውም ድሬዳዋ ያላትን ዕምቅ አቅም በቴክኖሎጂ በሚገባ ለመጠቀም ይህ ኤክስፖ ትልቅ አበርክቶት እንደሚኖረው ተናግረዋል ።
ኤክስፖው በዋነኝነት ድሬደዋን የአፍሪካ የቴክኖሎጂ መናኸሪያ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተገልጿል ።
ለአምስት ቀናት በሚካሄደው ኤክስፖው ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ ከ200 በላይ የመንግስትና የግል ድርጅቶች ፤ 100 የሚደርሱ ታላላቅ የውጪ የቴክኖሎጂ ተቋማት እንዲሁም ከ50 በላይ ኢንተርፕራይዞች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።
ትልቅ ዓላማን አንግቦ የሚካሄደው ይህ ዓለም ዓቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከስካይ ሊንክ የቴክኖሎጂ ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው ።
በድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ማዕከል የሚካሄደውን ይህን ኤክስፖ ከ40 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ይታደሙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል ።
ፕራይም ሚዲያ ኀብታሙ ምትኩ