ድሬደዋ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ልታስተናግድ ነው

2023-11-19
Event Image

ድሬደዋ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ልታስተናግድ ነው
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከስካይሊንክ ቴክኖሎጂስ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በድሬደዋ ከተማ እንደሚያዘጋጁ አስታወቀ።
በአዲስአበባ ከተማ ኢንተርሌግዥሪ ሆቴል በዛሬው ዕለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተጠቀሰው ‘’ከሃሳብ እስከ ትግበራ’’ በሚል መሪ ቃል ከጥር 15 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ድሬዳዋ በሚገኘው ወጣቶችና ስፖርት ማዕከል፣ ከሁሉም ክልል የሚመጡ ከ200 በላይ የመንግስት እና የግል ድርጅቶች እንዲሁም 100 የሚደርሱ የውጭ አገር የቴክኖሎጂ ተቋማት፣ ከ50 በላይ ኢንተርፕራይዝ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ኤክስፖ ይካኼዳል። ይህ ኤክስፖ ለ5 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በቆይታውም ከ40 ሺ በላይ ሰዎች እንደሚጎበኝ ይጠበቃል።
ድሬ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በኢትዮጵያ ትልቁና እንዲሁም በድሬደዋ ከተማ የመጀመሪያ የሆነ ሰፊ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ነው።
ይህ ኤክስፖ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የግሉ እና የመንግስት የቴክኖሎጂ ምርትና አገልግሎት አቅራቢዎች፣ ፣ ከሀገር ውጭ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ተቋማት እና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ለንግድ ወይም ለሕዝብ ጥቅም እንዲሁም ልዩ የሆኑ መፍትሄዎችን የሚሰጡ የፈጠራ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ኤክስፖ ኩባንያዎች ንግዶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ የሚሰሩትን የሚያሳዩበት ፣ ከአምራቾች፣ አቅራቢዎች እና ደንበኞች ጋር የሚገናኙበትን እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለከተማውም ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚያስገኝ ታምኖበታል ተብሏል።
አቶ ከድር ጁሀር የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ በመርሐግብሩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ድሬደዋ በባቡር፣ በስልክ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም የቴክኖሎጂ ተቋዳሽ የነበረች ከተማ መኾኗን አስታውሰዋል። ይኸን ለማስቀጠል ዓለም አቀፍ ኤክስፖው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው በመጥቀስ ለስኬቱ መገናኛ ብዙሃን የድርሻቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።
ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች ባደረጉት ንግግር ለኤክስፖው ስኬት የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።(በድሬቲዩብ ሪፖርተር)