ጎግል ማይክሮሶፍትና ሁዋዊ በመጀመሪያው “ድሬ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ” እንደሚሳተፉ ተገለጸ

2023-11-21
Event Image

1ኛው የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በድሬዳዋ ከተማ ከጥር 15 ጀምሮ ይከናወናል
በክልሎች ደረጃ በዓይነቱ እና በይዘቱ ቀዳሚ እንደሆነ የተነገረለት “1ኛው ድሬ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ” (1st Dire International Tech Expo) በድሬዳዋ ከተማ ሊከናወን መሆኑን ትናንት ህዳር 8 2016 ዓ.ል በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ተገለፀ። በኤክስፖው ጎግል፣ ማይክሮሶፍትና ሁዋዊም እንደሚሰተፉ ተነግሯል።
ከጥር 15-19 ቀን 2016 ዓ.ል እንደሚከናወን የተገለፀው ይህ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሰማሩ አገር በቀል እና የውጭ ተቋማት በስፋት እንደሚሳተፉበት ተጠቁሟል። ከሁሉም ክልል የሚመጡ ከ200 የመንግስት እና የግል ድርጅቶች እንዲሁም 100 የሚደርሱ የውጭ አገር የቴክኖሎጂ ተቋማት ከ50 በላይ ኢንተርፕራይዝ ድርጅቶች ይሳተፉበታል።
ኤክስፖው ለ5ቀናት የሚቆይ ሲሆን በቆይታውም ከ40,000 በላይ ጎብኚዎች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል።
ይህ በኢትዮጵያ ትልቁና በድሬደዋ ከተማ የመጀመሪያ የሆነ ሰፊ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ሲሆን በሀገር ውስጥ የሚገኙ የግል እና የመንግስት የቴክኖሎጂ ምርትና አገልግሎት አቅራቢዎች፣ ከሀገር ውጭ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ተቋማት እና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ለንግድ ወይም ለሕዝብ ጥቅም እንዲሁም ልዩ የሆኑ መፍትሄዎችን የሚሰጡ የፈጠራ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ኤክስፖ ኩባንያዎች ንግዶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ የሚሰሩትን የሚያሳዩበት ፣ ከአምራቾች፣ አቅራቢዎች እና ደንበኞች ጋር የሚገናኙበትን እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለከተማውም ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚያስገኝ ይገመታል ተብሏል።
ክቡር አቶ ከድር ጁሀር የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፣ የተከበሩ አቶ ኢብራሂም ዪሱፋ የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርጫፍ ኃላፊ፣ የተከበሩ አቶ ሻኪር አህመድ ብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኋላፊ፣ አቶ ገበየሁ ጥላሁን የከንቲባ ጽ/ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካዮች፣ የኢትዮጵያን ኤርላይንስ ግሩፕ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ሁሉም በዚህ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ኣካላት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ጊዜ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ትልቅ ሥራ እየሠራ ከሚገኘውና ታዋቂው ስካይሊንክ ቴክኖሎጂስ ጋር በጋራ በመሆን (Idea to Reality) ‘’ከሃሳብ እስከ ትግበራ’’ በሚል መሪ ቃል ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ድሬዳዋ በሚገኘው ትልቁ ወጣቶችና ስፖርት ማዕከል ይከናወናል።
አቶ ሙሐመድ ከረም የስካይሊንክ ቴክኖሎጂ ሥራ አስፈጻሚ ኤክሰፖውን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።